ተመድ፡ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በጣም እንዳሳሰበው ገለጸ
ቃል አቀባይ እስቴፋን ዱጃሪክ፡ ሁሉም ወገኖች ጥቃትን አቁመው ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲመለሱ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ እስቴፋን ዱጃሪክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡ ዋና ጸሐፊው በትግራይ፡ አፋርና አማራ ክልሎች የሚካሄደው ጦርነት በጣም እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፡ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች በአስቸኳይ ጠብ አጫሪ ተግባራቸውን አቁመው፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች በስምምነቱ መሠረት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ጠይቀዋል።
ዋና ጸሐፊው አካባቢውን ወደ ከፋ ግጭት ሊመሩ የሚችሉ ተግባራትን እንደማይደግፉ በመግለጽ፡ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል የሚሉ ሪፖርቶች እንዳሳሰቧቸው አስታውቀዋል።
በአካባቢው የሚገኙ አገራት በሙሉ በአንድ አገር ሉዓላዊ ግዛት ወይም የፖለቲካ ነጻነት ላይ ኃይል ከመጠቀምና ከማስፈራራት የሚከለክለውን የተመድ ቻርተር እንዲያከብሩና በሌሎች ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ጠይቀዋል። ጽሕፈት ቤታቸው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።
