ሳውዲ ዓረቢያ የሁቲ ጥቃቶችን መጠን አመነች
ጥቃቱ ከተጠበቀው በላይ መሆኑን በሳውዲ የሚመራው ጥምረት ቃል አቀባይ ቱርኪ አል-ማልኪ ገለጹ።

በሁቲ ታጣቂ ቡድን በሳውዲ ዓረቢያ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ዒላማዎች ላይ ሲፈጸም የቆየው የባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃት ከተጠበቀው በላይ መሆኑንና ሪያድ ራሷን ለመከላከል የተቻላትን እያደረገች መሆኑን በሳውዲ የሚመራው ጥምረት ቃል አቀባይ ቱርኪ አል-ማልኪ ጥቅምት 15 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመኑ።
ሁቲ በበርካታ የየመን አካባቢዎች እየገሰገሰ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ቡድኑ ወደ 70 በመቶ የሚጠጋውን የየመን ግዛት መቆጣጠሩን ጠቅሰዋል።
በርካታ የክልሉ አገሮች በዚህ ቡድን በኩል ክልላዊ ጥቅማቸውን ለማስፈጸም እየሞከሩ መሆኑን የገለጹት አል-ማልኪ፣ ሁቲ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ በክሩዝና በባሊስቲክ ሚሳይሎች ትላልቅ የሳውዲ ከተሞችን ዒላማ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሁቲ ቡድን በበኩሉ በኃይሎቹ ላይ የሚደረገው የጥምረት ድብደባ ካልቆመ የARAMCO ተቋማትን አንድ በአንድ እንደሚያወድም አስጠንቅቋል።
