ሑቲ በባብኤልመንደብ መሬት ካጣ በኋላ በአብሃ አየር ማረፊያ ጥቃት ፈጸምኩ አለ
የየመን መንግሥት ኃይሎች በመጻብቦው ዙሪያ ገስግሰው የወደብ ከተማዋን ሞቻ ተቆጣጥረዋል።

የሳውዲ አረቢያ የሲቪል አቪዬሽን ጠቅላይ ባለሥልጣን ሰኞ ጥቅምት 5 ምሽት በጃዛን የሚገኘው የኪንግ አብደላ ቢን አብዱልአዚዝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና የነጅራን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው፣ ሦስት ቀላል የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት እንደደረሰ፣ የተጎዱትም በሆስፒታል ሕክምና እንደተደረገላቸው ገልጿል። ውድመቱን ለመገምገምና የተቋማቱን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። በሳውዲ የዜና አገልግሎት የተሰራጨው መግለጫ ስለአብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ያለው ነገር የለም።
የሑቲ ቡድን፣ ማክሰኞ ጥቅምት 6 በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኘው የአብሃ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።
የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ፣ ሚሳይሉ አየር ማረፊያውን በቀጥታ በመምታት የአውሮፕላኖችን እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን ገልጸው፣ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በሳዑዲ ዓረቢያ የአየር ክልል በረራ እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ የተሰማው፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚደገፉ የየመን መንግሥት ኃይሎች ሰኞ በባብኤልመንደብ መጻብቦ ዙሪያ ኃይለኛ ግስጋሴ አድርገው የሞቻ ከተማ ጫፍ ላይ ከደረሱ በኋላ ነው። የየመን መከላከያ ሚኒስቴር የወደብ ከተማዋ በቁጥጥሩ ሥር መግባቷን ገልጿል።
ከሳዑዲ ዓረቢያ በኩል ስለተባለው ጥቃት እስካሁን የወጣ ቀጥተኛ መግለጫ የለም።
