ቱርክ፣ ቀጠር፣ ፓኪስታንና ኢንዶኔዥያ የባድር ስምምነት ፈረሙ
በዶሃ የተፈረመው ስምምነት በወታደራዊ ቁሳቁስ ምርትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያተኮረ ነው።

ቱርክ፣ ቀጠር፣ ፓኪስታንና ኢንዶኔዥያ በጋራ ወታደራዊ ቁሳቁስ በማምረት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በምርምርና ልማት ተግባራት ላይ ያተኮረ፣ የባድር ስምምነት በመባል የሚታወቅ ውል ጥቅምት 21 በዶሃ መፈራረማቸው ተገልጿል።
ስምምነቱ የአራቱን አገራት የኢንዱስትሪ አቅም ለማቀናጀትና የወታደራዊ ቁሳቁስ አቅርቦት ሰንሰለትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ሌሎች አገራት ወደ ስምምነቱ እንዲቀላቀሉ የሚያስችል አሠራር እንዳለውም ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።
ስምምነቱ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ትብብር ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ፣ በአባል አገራት ላይ የትጥቅ ጥቃት ቢፈጸም የጋራ የመከላከል ግዴታ እንደማይጥል ተንታኞች ያስረዳሉ። ይህ ስምምነት በነሐሴ በቱርክ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በፓኪስታን መካከል የተፈረመውን የመካ ስምምነት ተከትሎ የመጣ ነው።
