የግጭት ታዛቢዎች የኤርትራ ሠራዊት ወደ አሰብ ወደብ በሚወስደው መንገድ ላይ፣ በቡሬ አቅራቢያ ተጨማሪ ኃይል ማስፈሩን ገለጹ
ክሪቲካል ትሬትስ ፕሮጀክት የሳተላይት ምስሎችንና ሁለት የግጭት ታዛቢዎችን ጠቅሶ አስታወቀ። አዲስ አበባም አስመራም እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ክሪቲካል ትሬትስ ፕሮጀክት ዓርብ ዕለት ባወጣው ሪፖርት፣ ሁለት የግጭት ታዛቢዎችና የሳተላይት ምስሎች የኤርትራ ሠራዊት ወደ አሰብ ወደብ በሚወስደው መንገድ አካባቢ ያሉትን ቦታዎቹን ማጠናከሩን እንደሚያመለክቱ ገለጸ። በአፋር ክልል በምትገኘው የቡሬ ከተማ አቅራቢያም ተጨማሪ ኃይል መስፈሩ ተገልጿል። ሪፖርቶቹ በገለልተኛ ወገን ሊረጋገጡ አልቻሉም።
ክሪቲካል ትሬትስ ፕሮጀክት ዓርብ ዕለት ባወጣው ሳምንታዊ የኢትዮጵያ ጦርነት ሪፖርት፣ ሁለት የግጭት ታዛቢዎችና የሳተላይት ምስሎች የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ወደ አሰብ ወደብ በሚወስደው አውራ ጎዳና አካባቢ በኢትዮጵያ-ኤርትራ ድንበር ላይ ያሉትን ቦታዎቹን ማጠናከሩን እንደሚያመለክቱ ገለጸ። ሪፖርቱ እንዳለው ዘ ኢትዮጵያን ኮንፍሊክት ማፕ የተባለው ታዛቢ ሐሙስ ዕለት፣ የኤርትራ ኃይሎች በአፋር ክልል ከምትገኘው የቡሬ ከተማ ከስምንት ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት በኤርትራ በኩል ባለው ድንበር ተጨማሪ ኃይል ማስፈራቸውን አስታውቋል። ታዛቢው ሳጂድ ናዲም ደግሞ ኅዳር 14 የኤርትራ ኃይሎች ወደ አሰብ እየተጓዙ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። ክሪቲካል ትሬትስ ፕሮጀክትና ኢንስቲትዩት ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ዎር፣ ከኅዳር መጀመሪያ ጀምሮ ቡሬንና አሰብን በሚያገናኘው መንገድ አጠገብ የተሽከርካሪ ዱካዎች መጨመራቸውን የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩ ገለጹ። ኢትዮጵያም ኤርትራም ስለተባሉት እንቅስቃሴዎች ያሉት ነገር የለም፤ ሪፖርቶቹም በገለልተኛ ወገን ሊረጋገጡ አልቻሉም።
