አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ ዘመቻ እያዘጋጁ መሆናቸው ተገለጸ
ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ሁለቱ አገራት አጭር ግን እጅግ አውዳሚ ወታደራዊ ዘመቻ እያዘጋጁ መሆናቸውን ዘግቧል።

በዘ ኒውዮርክ ታይምስ አዲስ ዘገባ መሠረት፣ አሜሪካና እስራኤል ኅዳር 3 ሊካሄድ ከታቀደው የአሜሪካ የመካከለኛ ዘመን ምርጫ በኋላ በኢራን ላይ ሌላ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ዝርዝር ዕቅድ እያዘጋጁ መሆኑ ተገልጿል።
ጋዜጣዋ የአሜሪካ ባለሥልጣናትንና ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮችን ጠቅሳ ባዘጋጀችው ዘገባ፣ ሁለቱ አገራት «አጭር ግን እጅግ አውዳሚ» ብለው የሚገልጹትን ዘመቻ ዝግጅታቸውን ማጠናከራቸውን አስታውቃለች።
ዋና ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ከተባሉ ቦታዎች መካከል የኢራን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ የኒውክሌር ተቋማትና የሚሳይልና ሰው አልባ አውሮፕላን ማከማቻዎች ይገኙበታል።
ቀጣዩ ከባድ የጥቃት ዙር የኢራንን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በማሽመድመድ አገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን እንድትቀበል ሊያስገድድ የሚችል አደገኛ እርምጃ እንደሚሆን ምንጮቹ አስጠንቅቀዋል። ትራምፕ በማንኛውም ጊዜ ሐሳባቸውን ሊቀይሩ የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም ዘገባው አመልክቷል።
