ትራምፕ፡ የሕዳሴው ግድብ ዓባይን ያለ ውሃ አስቀርቶታል አሉ
ግድቡ በአሜሪካ ገንዘብ ተሠርቷል አሉ፤ ኢትዮጵያ ይህን አጥብቃ ትቃወማለች

አሕራም ኦንላይን ባሰራጨው መረጃ፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዓባይን ያለ ውሃ አስቀርቶታል በማለት ትችታቸውን ማሰማታቸውን ገልጿል።
ትራምፕ በመግለጫቸው፡ በኢትዮጵያ የተሠራው ከዓለም ትልልቅ ግድቦች አንዱ በአሜሪካ ገንዘብ መሠራቱን በመግለጽ፡ ሁሉንም ውሃ ከዓባይ እየወሰደ ነው ብለዋል። ግብጻዊ ሆነህ ዓባይ ውሃ አልባ መሆኑ ጥሩ አይደለም፡ ሆኖም በጉዳዩ ላይ እየሠራሁ ነው ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ሲሰጡ የመጀመሪያቸው አይደለም፤ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸውም ስለዚህ ግድብ ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ወጪ መሠራቱን ይከራከራል፤ የዓባይ ውሃ አልቋል የሚለውንም በመቃወም ኃይል በማመንጨት ወደ ዓባይ የሚደረገው የውሃ ፍሰት እንዳልተቋረጠ ትገልጻለች። ግብጽ በበኩሏ ግድቡን እንደ ትልቅ ስጋት ትመለከተዋለች።
