በሱዳን የድሮን ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎችን ገደለ
በአቡ ሻንዲ ሴቶችና ሕፃናት ይገኙበታል፤ ድሮኑ ከኢትዮጵያ መምጣቱ ተነግሯል
ማክሰኞ ጥቅምት 6 በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት በስደተኞች ካምፕ አካባቢ በተፈጸመ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት፡ ሴቶችና ሕፃናት ጨምሮ ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን የግዛቱ ባለሥልጣናትና የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል።
ጥቃቱ ከደማዚን በስተምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት በዋድ አልማሂ አካባቢ በሚገኘው አቡ ሻንዲ በተባለ ቦታ መፈጸሙንና አብዛኞቹ ተጎጂዎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንደነበሩ የአገሪቱ የዜና ማሰራጫዎች አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸውን የሚገልጽ የመጀመሪያ ሪፖርት እንደደረሰው ሲገልጽ፡ የሱዳን ሐኪሞች በበኩላቸው 31 ሰዎች መሞታቸውንና 19 መቁሰላቸውን አስታውቀዋል። ባለሥልጣናትና ሐኪሞች ጥቃቱን የፈጸሙት የዳዕመል ሰሪዕ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዋድ አልማሂ አስተዳዳሪ ማሕሙድ አልሸኽ ለኤኤፍፒ በሰጠው መረጃ፡ ሰው አልባ አውሮፕላኑ ከኢትዮጵያ ውስጥ መምጠቁን ገልጿል። የሱዳን የሐኪሞች መረብ በተጨማሪ፡ ጥቅምት 3 በኡም ባድር 25 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
