በሱዳን የድሮን ጥቃት 41 ሰዎችን ገደለ
አብዛኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፤ ተመድ ጥቃቱን አውግዟል

በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን በብሉ ናይል ግዛት፡ ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አቡ ሻንዲ አካባቢ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ በተፈጸመ ከባድ የድሮን ጥቃት፡ 41 ሰዎች ተገድለው በርካቶች ቆስለዋል።
በጦርነቱ ተፈናቅለው ጥገኝነት በጠየቁ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸመ ጥቃት በመሆኑ፡ አብዛኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸው ተገልጿል።
የመብት ተሟጋች ቡድን Emergency Lawyers፡ ጥቃቱን የፈጸመው ከሱዳን ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው ራፒድ ሳፖርት ኃይል መሆኑን አስታውቋል፤ ኃይሉ ግን እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ድርጊቱን አጥብቆ አውግዟል፤ ዩኒሴፍም ከሟቾቹ አምስቱ ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት መሆናቸውን ገልጿል።
