በደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ ስደተኞች ላይ የተደረገ ሰልፍ ወደ ብጥብጥ ተቀየረ
በጆሃንስበርግ፡ ደርባንና ሶዌቶ በርካታ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል

በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሕገወጥ ስደተኞች ላይ የተጀመረው አዲስ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ብጥብጥ በመሸጋገሩ ከባድ የንብረት ውድመት መድረሱን የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል።
ሰልፈኞቹ በጆሃንስበርግ፡ ደርባንና ሶዌቶ ባደረጉት ሰልፍና በተከተለው ሁከት፡ በርካታ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ተገልጿል። በውጭ ዜጎች በሚተዳደሩ በርካታ ተቋማት ላይ ዝርፊያ መፈጸሙም ተነግሯል።
ይህ አዲስ ሁከት፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በባዕዳን ጥላቻ ምክንያት የተከሰተውን ተመሳሳይ ክስተት ተከትሎ የመጣ ነው። በመጀመሪያው ሁከት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰው ነበር።
ሕገወጥ ስደተኞች ለሥራ አጥነት ምክንያት ናቸው የሚሉ ደቡብ አፍሪካውያን፡ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ሁሉ እንዲወጡ ሲጠይቁ ቆይተዋል። አብዛኞቹ ስደተኞች የዚምባብዌ፡ የሞዛምቢክ፡ የማላዊና የናይጄሪያ ዜጎች መሆናቸው ይገለጻል።
