የሳውዲ ጥምረት በያንቡ የተተኮሰ ሚሳይል መከላከሉን አስታወቀ
አራት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መምታቱን የገለጸው ጥምረት፣ በዓደን ሁለት ሚሳይሎች በአውሮፕላን ማረፊያው ወድቀዋል።

በየመን በሳውዲ ዓረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል ጥቅምት 16 ማምሻውን ወደ ምሥራቃዊና ደቡባዊ ሳውዲ ዓረቢያና ወደ ሪያድ ይበሩ የነበሩ በድምሩ አራት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መምታቱንና ወደ ወደብ ከተማዋ ያንቡ የተተኮሰውን ባሊስቲክ ሚሳይል ማክሸፉን አረጋገጠ።
ጥምረቱ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። በዚህ ሳምንት ሐሙስ በመዲና ክልል ላይ የተተኮሰ ክሩዝ ሚሳይልንም መከላከሉን ገልጿል።
የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ ግን ቡድኑ ሐሙስ በሳውዲ ግዛት ላይ ጥቃት አለመፈጸሙን ገልጸው ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
በዚያው ዕለት በዓደን ሁለት ሚሳይሎች በአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ግቢ መውደቃቸውን የከተማዋ የጸጥታ ክፍል አስታውቋል።
