ጉተሬዝ፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በአስቸኳይ ይቁም አሉ
የኤርትራ ኃይሎች ስለመግባታቸው የሚገልጹ ሪፖርቶች ተጨማሪ ስጋት እንዳሳደሩበት ጠቁሟል
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፡ በትግራይ፡ አፋርና አማራ ክልሎች እንደገና በተቀሰቀሰው ግጭት ዙሪያ ጥልቅ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ዓርብ ጥቅምት 9 በወጣው መግለጫ፡ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ወገኖች ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ወደ ድርድር እንዲመለሱ አጥብቀው መማጸናቸውን ቃል አቀባያቸው እስቴፋን ዱጃሪክ አስታውቀዋል።
ዋና ጸሐፊው፡ የኤርትራ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ስለመግባታቸው የሚገልጹ ሪፖርቶች ተጨማሪ ስጋት እንደፈጠሩባቸው በመጠቆም፡ የአካባቢው አገራት በሙሉ በተመድ ቻርተር መሠረት በሌላ አገር የግዛት አንድነት ወይም የፖለቲካ ነጻነት ላይ ኃይል ከመጠቀምና ከማስፈራራት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በመጨረሻም፡ ተጽዕኖ ያላቸው አገራት ውጥረቱን ለማርገብ እንዲሠሩ ጠይቀው፡ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሽምግልና አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
