ግብጽ በቀይ ባሕር እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗ ተገለጸ
የኢትዮጵያ እንቅስቃሴዎች የአካባቢውን ጸጥታ አደጋ ላይ ቢጥሉ እጇን አጣጥፋ አትመለከትም ተብሏል
ግብጽ፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች የቀይ ባሕርና የቀንደ አፍሪካ ጸጥታን በቀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ ከሆኑ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗ ተገልጿል።
ግብጽ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ፡ ከትግራይ ግጭትና ከኤርትራ ጋር ካላት ውጥረት ባሻገር፡ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን የግብጽ ጋዜጠኛ አሽራቅ አልአውሳጥ ካልድ ማሕሙድ ገልጿል።
ጋዜጠኛው፡ በቀይ ባሕር ዳርቻ አዲስ ወታደራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ወይም የኤርትራን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ፡ በአካባቢው የኃይል ሚዛንና የባሕር ጸጥታ እንዲሁም በግብጽ ከኤርትራ፡ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳለው አስረድቷል።
ግብጽ በእጇ በርካታ አማራጮች ስላሏት፡ በዚህ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ባለው አካባቢ የኃይል ሚዛንን ለመቀየር የሚደረግ ሙከራን እጇን አጣጥፋ የምትመለከትበት ዕድል እንደሌለ የተናገረው ጋዜጠኛው፡ ሊገባበት የታሰበው ጦርነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለአሥርት ዓመታት አውዳሚ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
