በፈረንሳይ በተማሪዎች ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል
ተማሪዎች የመምህራን እጥረትን፣ በክፍሎች ውስጥ ከአቅም በላይ መጨናነቅንና ያረጁ የትምህርት ቤት ሕንጻዎችን በመቃወም ላይ ናቸው

በፈረንሳይ ተማሪዎች የመምህራን እጥረትን፣ በክፍሎች ውስጥ ከአቅም በላይ መጨናነቅንና ያረጁ የትምህርት ቤት ሕንጻዎችን በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል፤ ተቃውሞው በመቀጠሉም በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
ተቃውሞው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በፓሪስ ከተጀመረ በኋላ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ተስፋፍቷል።
የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር 65 የትምህርት ቤት ሠራተኞችና 40 መምህራን መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም በማክሰኞ ዕለት ብቻ 1,949 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁሉም ተማሪዎች መሆናቸው እርግጠኛ እንዳልሆነና አውቶቡሶችን ዒላማ ማድረግና ትምህርት ቤቶችን በእሳት ማቃጠል የመሳሰሉ ድርጊቶች ሁኔታው ከተቃውሞ አልፎ መሄዱን የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን 100 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
