የአውሮፓ ኅብረት፦ በቀጣናው ያለው ውጥረት ሰፊ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲል አስጠነቀቀ
የውጭ ተዋናዮች ከጣልቃ ገብነት እንዲታቀቡና በሁሉም ግንባሮች ውጥረቱ እንዲረግብ ጠይቋል።

የአውሮፓ ኅብረት ጥቅምት 5 ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለው ግጭትና በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየታየ ያለው ከፍተኛ ውጥረት ሰፊ ቀጣናዊ ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል አስጠነቀቀ።
ይህም በመላው የአፍሪካ ቀንድ ላይ በሰላምና በመረጋጋት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል።
ኅብረቱ በሁሉም ግንባሮች አስቸኳይ የውጥረት ማርገብ እንዲደረግና ተሳታፊ አካላት ውጥረቱን ከሚያባብሱ ተግባሮችና ንግግሮች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል፤ የፕሪቶሪያ ቀዋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተዋዋይ ወገኖችም በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ሥር ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እንደገና ቃል ሊገቡ ይገባል ብሏል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ እንዲከበር፣ ሲቪል ዜጎች እንዲጠበቁና የሰብአዊ ድጋፍ ያለ ገደብ እንዲደርስ የጠየቀው ኅብረቱ፣ የሁሉም አገሮች ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበትና የውጭ ተዋናዮች ከጣልቃ ገብነት መታቀብ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል።
