የአውሮፓ ኅብረት፦ ሁለት አባል ሀገራት መርከቦቻቸውን ወደ ቀይ ባሕር ለመላክ ተዘጋጅተዋል
ካያ ካላስ የሀገራቱን ስም ሳይጠቅሱ፣ የሑቲ ጥቃቶች የአስፒደስ ተልዕኮ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ አድርገውታል ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ካያ ካላስ፣ ሁለት አባል ሀገራት በቀይ ባሕር የሚፈጸሙ የሑቲ ጥቃቶችን ለመከላከል መርከቦቻቸውን ለመላክ መዘጋጀታቸውን የሚያመለክቱ ምልክቶች መኖራቸውን ገለጹ።
ሰኞ መስከረም 28 ቀን በብራስልስ የአውሮፓ ኅብረት የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ሀገራቱ ተጨማሪ መርከቦችን ማቅረብ እንደሚችሉ በስብሰባው ማመልከታቸውን ተናግረዋል፤ የሀገራቱን ስም ግን አልጠቀሱም።
እያደገ የመጣው የሑቲ ጥቃት መጠን የኅብረቱ የቀይ ባሕር ተልዕኮ — የአስፒደስ ዘመቻ — በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ አድርጎታል ሲሉ አስረድተዋል።
ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የንግድ መርከቦች፣ ኅብረቱ አጀብ ለማድረግ ከሚያስችሉት የጦር መርከቦች በቁጥር እንደሚበልጡም ገልጸዋል።
ፈረንሳይ ተጨማሪ አጀብ ወደ ቀይ ባሕር ማሰማራቷንና ሌሎች አባል ሀገራት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቧ፣ እንግሊዝ ደግሞ የአውሮፕላን ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።

