ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ልኡክ በካይሮ፤ ግብፅ ለኤርትራ ልማት አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ገለጸች
በሕግደፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሓጎስ ገብረሂወትና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ነስረዲን በከት የተመራው ልኡክ፣ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ባድር ዓብደላቲ ጋር ተገናኝቷል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቶችና በኢንቨስትመንት ስምምነቶች ላይ ውይይት ያደረገው ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ልኡክ፣ አሁን ግብፅ መግባቱ ተገለጸ።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ባድር ዓብደላቲ፣ በሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሓጎስ ገብረሂወትና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ነስረዲን በከት የተዋቀረውን ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ልኡክ ካገኙ በኋላ፣ ግብፅ የኤርትራ መንግሥት በሚያደርገው የብሔራዊ ልማት ጥረት ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ በተለይም በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ከኤርትራ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለማጥለቅ ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውን የአገሪቱ ዘገባዎች አረጋግጠዋል።
ግብፅ ለኤርትራ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሙሉ ድጋፍ እንዳላት ለኤርትራ ልኡክ በድጋሚ ያረጋገጡት ሚኒስትር ዓብደላቲ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ልውውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግና ንግድንና የጋራ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተውበታል።
ግብፅ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ቴክኒካዊ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ግብፃዊው ሚኒስትር፣ የግብፅ የግል ኩባንያዎች በኤርትራ ገበያዎች ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ኢንቨስት እንዲያደርጉ አበረታተዋል።
በካይሮ ከተማ በተደረገው ውይይት፣ ሁለቱ አገራት በየተራ በአስመራና በካይሮ የሚያካሂዱትን የምክክር መድረኮች ያካተተ፣ በሁለትዮሽ ጉዳዮችና የጋራ ትኩረት በሚሰጣቸው ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ፣ በተለይም በሱዳንና በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታዎችና በቀይ ባሕር ደኅንነት ላይ ጥልቅ ውይይት መደረጉን የአገሪቱ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ ወገኖች፣ በኤርትራና በግብፅ መካከል ያለው የቀጠለ ጠንካራ ግንኙነት ከቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ዋና ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በኢነርጂና በጤና ዘርፎች የበለጠ ለማሳደግ መስማማታቸውም ተገልጿል።
የከፍተኛው የኤርትራ መንግሥት ልኡክ የግብፅ ጉብኝት፣ በቅርቡ በቀጣናው የተፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎችና በቀይ ባሕር ቀጣና ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ኤርትራ ከግብፅ ጋር ጥልቅና ውጤታማ ትብብር እያደረገች መሆኑን የሚያመለክት ነው።
