አሜሪካ በእርዳታ ተሽከርካሪዎች ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት አወገዘች
ዋሽንግተን፡ በትግራይ በእርዳታ መኪኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲመረመር ጥሪ አቀረበች።

የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ በማጓጓዝ ላይ የነበሩ የካቶሊክ ረሊፍ ሰርቪስ የእርዳታ ድርጅት ተሽከርካሪዎች ላይ የተፈጸመውን ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታወቀ።
የአሜሪካ የውጭ እርዳታ ድርጅትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚገኘው የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በእርዳታ ሠራተኞችና እርዳታ በሚያጓጉዙ መኪኖች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በአስቸኳይ ጥልቅ ምርመራ እንዲያካሂዱ፣ ውጤቱንም ለሕዝብ በይፋ እንዲገልጹ እንዲሁም ድርጊቱ እንዳይደገም እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ተደርጓል።
በተጨማሪም፣ ለተቸገሩ ሰዎች ያለ ምንም እንቅፋት ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የመገናኛ መስመሮች ክፍት ሆነው መቀጠል አለባቸው ሲል አስገንዝቧል።
