ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት 3 ቅድመ ሁኔታዎች አቀረበች
አሜሪካ ጥያቄዎቹን ከተቀበለች፣ ወሽመጡ በሰባት ቀናት ውስጥ ይከፈታል ትላለች ኢራን።

ኢራን ከዓለም ዋና ዋና የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመክፈት፣ ለአሜሪካ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች አቀረበች።
አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የባሕር ኃይል እገዳና በነዳጅ ሽያጭ ላይ ያለውን ማዕቀብ ካነሳች፣ እንዲሁም ሊባኖስን ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነትን ከተቀበለች፣ ኢራን በ7 ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደምትከፍትና በኒውክሌር መርሐ ግብሯ ዙሪያ ድርድር በድጋሚ እንደምትጀምር ገልጻለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዓርብ መስከረም 25 በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት መግቢያ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የ7 ቀናቱ የጊዜ ሰሌዳ የሚጀምረው አሜሪካ ጥያቄዎቹን ከተቀበለችበት ሰዓት ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያዎቹ ዝግጅቶች ከ4 እስከ 5 ቀናት እንደሚወስዱና ወሽመጡም በስድስተኛው ቀን ሙሉ በሙሉ ክፍት እንደሚሆን አስረድተዋል። በሰባተኛው ቀን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የመጨረሻው ድርድር እንደሚጀምር ገልጸዋል።
20 በመቶ የዓለም የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ የሚያልፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ በኢራን መዘጋቱ አገሪቱ የምትጠቀምበት ዋና የዓለም አቀፍ ጫና ማሳረፊያ መሣሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።
ዋይት ሐውስ በሰጠው አጭር ምላሽ፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አወንታዊና ገንቢ ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን ብቻ አስታውቋል።

