የኢራን ፕሬዚዳንት በተባበሩት መንግሥታት አሜሪካንና እስራኤልን አስጠነቀቁ
መሱድ ፔዜሽኪያን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የማልማት ዓላማ እንደሌላት ገልጸዋል፤ የኒውክሌር ሳይንስ እንቅስቃሴዋን ግን እንደማታቆም አስታውቀዋል።

በ81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢራን ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን፣ አሜሪካንና እስራኤልን በሠሩት ተግባር እንዲጸጸቱ እናደርጋቸዋለን ሲሉ አስጠነቀቁ።
አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የማልማት ዓላማ እንደሌላት በመግለጽ፣ የኒውክሌር ሳይንስና ሰላማዊ ቴክኖሎጂን የማልማት እንቅስቃሴዋን ግን እንደማታቆም ለጉባኤው ተሳታፊዎች በድጋሚ በይፋ አስታውቀዋል።
ኢራን የኒውክሌር እውቀት በጥቂት አገራት ቁጥጥር ሥር እንዲሆን እንደማትቀበል የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ አገራቸው የመካከለኛው ምሥራቅን የባሕር ጸጥታ አንድ ወገን ብቻ እንዲቆጣጠር እንደማትፈቅድ፣ አገራቸውን ለመከላከል ከሆነም ከማንኛውም ጦርነት እንደማይፈሩና በተመሳሳይ ጊዜም የሰላም ድርድርን ወደ ጎን እንደማይተዉ ገልጸዋል።
እኛ አገራችንን መከላከል ነው የምንፈልገው እንጂ ሌሎች አገራትን መውረር አይደለም ሲሉ አክለዋል። የአቶሚክ ቦምብ የያዘችው እስራኤል ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ግን ወደ ኢራን መግባታቸውን በመጥቀስ፣ እስራኤል ትገድላለች፤ ኢራን ደግሞ ማዕቀብ ይጣልባታል ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉባኤው ላይ ኢራንን ያስፈራራ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ፔዜሽኪያን ይህን አስመልክተው፣ ይህ በኃይልና በጫና የመግዛት ምልክት ነው በማለት፣ የአገራቸው ጠላቶች ጫና ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ኢራን ወራሪዎቿን በተግባራቸው እንዲጸጸቱ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ሁኔታ ዙሪያም፣ አንዲትም አገር በራሷ ብቻ ዋስትና እንደማይኖራት በመግለጽ፣ ጸጥታን በጋራ እንገነባለን፤ ስናጣውም መዘዙን በጋራ ነው የምንጋፈጠው ሲሉ ለጎረቤት አገራት የሚመለከት መልእክት አስተላልፈዋል።
