ግብፅ የሶማሊያን ልዩ ኮማንዶ ኃይሎች አስመረቀች
ሥልጠናው የኮማንዶ ሥራዎችን፣ የጸረ-ሽብር ዘመቻን፣ የከተማ ውጊያንና ከአውሮፕላን በመዝለል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አካትቶ ነበር።

ግብፅና ሶማሊያ በደረሱበት የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መሠረት፣ በካይሮ ሥልጠና እየተከታተሉ የነበሩ የሶማሊያ ሠራዊት ልዩ ኮማንዶ አባላት መመረቃቸውን የአገሪቱ ዘገባዎች ገልጸዋል።
የግብፅ መንግሥት የሶማሊያን ብሔራዊ ሠራዊት ለማጠናከር በሚል ዓላማ እነዚህን ኮማንዶዎች ማሠልጠኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ሥልጠናው የኮማንዶ ሥራዎችን፣ የጸረ-ሽብር ዘመቻን፣ የከተማ ውስጥ ሥራዎችንና እንዲሁም ከአውሮፕላን በመዝለል የሚደረጉ ወታደራዊ የፓራሹት እንቅስቃሴዎችን ያካተተ መሆኑን የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
የሶማሊያ ልዩ ብሔራዊ ሠራዊት አዛዝ ብርጋዴር ጄነራል አዳን መሐመድ ዑመር፣ ሐሙስ መስከረም 24 ቀን በካይሮ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አባላቱ በመላ አገሪቱ በሚሰማሩበት ወቅት ያገኙትን ልዩ ክህሎት በተግባር እንዲያውሉ አሳስበዋል።
የግብፅ ባለሥልጣናት፣ የዚህ ሥልጠና ዋና ምክንያት በአልሸባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ኃላፊነት የሚወስዱና ብቁ የሆኑ የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎችን ለመገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ክንውን፣ ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር በከባድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ በምትገኝበትና በሶማሊያ ሰፊ ተሳትፎ ለማድረግ በምትሠራበት ወቅት በመምጣቱ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።

