በሱዳን በሲቪል ዜጎች ላይ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት ተባብሷል
በአቡ ሻንዲ 41 ሰዎች ሲገደሉ፡ በአልደባብ ደግሞ ከ80 በላይ ሞተዋል።

ባለፈው አርብ በሱዳን ሰማያዊ አባይ ግዛት፡ ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ አቡ ሻንዲ በተባለ ስፍራ፡ ከጦርነት ሸሽተው መጠለያ በሚፈልጉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የሟቾች ቁጥር 41 ደርሷል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን የድንገተኛ ጊዜ ጠበቆች እንደገለጸው፡ በጥቃቱ ስምንት ሕፃናት ይገኙበታል።
እሁድ ደግሞ በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት በምትገኘው አልደባብ ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 80 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። 47 የቆሰሉ ወደ አልሙጅላድ መወሰዳቸውንና ከእነርሱም 30 ያህሉ በሕይወት መቆየት አለመቻላቸውን የሕክምና ምንጭ ተናግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት በመላው ሱዳን እየጨመረ የመጣውን ገዳይ የድሮን ጥቃት እንደሚያወግዝ ገልጿል። ቃል አቀባዩ ስቴፋን ዱጃሪክ፡ በምዕራብ ዳርፉር፡ በደቡብና በሰሜን ኮርዶፋን 10 ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 19 ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሰዋል።
የእርዳታ ድርጅቶች ግን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ከመግለጫ የዘለለ አለመሆኑን ይተቻሉ።

