አምስት የሕወሓት ኮሎኔሎች ለትግራይ ሰላም ኃይል እጃቸውን ሰጡ
እጅ መስጠቱ በሰሜን ትግራይ በዕንቲጮ ዞን በሚገኘው መመን በተባለ ቦታ መፈጸሙ ተገልጿል።

ከሕወሓት ጎን የቆመው የትግራይ ኃይል አምስት ከፍተኛ የጦር መሪዎች በሰሜን ትግራይ በዕንቲጮ ዞን በሚገኘው መመን በተባለ ቦታ ለትግራይ ሰላም ኃይል (TPF) እጃቸውን መስጠታቸው ተገለጸ።
ከእነዚህ ከፍተኛ መሪዎች ጋር ተጨማሪ የበታች መኮንኖችም እጃቸውን መስጠታቸው ተነግሯል።
የመሪዎቹ ስም፡ ኮሎኔል በርሀ ገብረመድኅን (ምክትል የጦር አዛዥ)፡ ኮሎኔል ወልዳይ ማውጫ (የሠራዊት ሎጂስቲክስ ኃላፊ)፡ ኮሎኔል ገብረማርያም ተክሉ (የኮር 2 አዛዥ)፡ ኮሎኔል መሓሪ ይፍተር (የኮር 2 ኮሚሳር) እና ኮሎኔል ገብረሃዋርያ ደስታ (የኮር 2 ሎጂስቲክስ ኃላፊ) ናቸው።
ይህ እጅ መስጠት የተከሰተው ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊትና በአጋሮቹ የTPF ኃይሎች የተካሄደውን ወታደራዊ እርምጃ ተከትሎ ነው። የፌዴራል ኃይሎች በቅርቡ ሽረን፡ ዓዲጋራትን፡ ዕዳጋ ሓሙስን፡ ዓጽብንና ፍረወይንን ሲቆጣጠሩ፡ ከሕወሓት ጎን የቆሙ ተዋጊዎች ከአካባቢዎቹ መሸሻቸው ይታወቃል።
