ኤርትራዊት ገበሬ ከዓለም 100 ጀግኒት ሴቶች አንዷ ተባለች
ወይዘሮ ሮዚና መብራህቱ ከ131 ሀገራት ከተወዳደሩ 600 ሴቶች ጋር ተፎካክራ አሸንፋለች።

ኤርትራዊት ገበሬ ወይዘሮ ሮዚና መብራህቱ፡ የዓለም የምግብ ቀን ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆና ከዓለም 100 የልማት ጀግኒት ሴቶች አንዷ ለመሆን መብቃቷን የኤርትራ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ወ/ሮ ሮዚና ለዚህ ሽልማት የበቃችው፡ ከ131 ሀገራት ከተወጣጡ 600 አርአያ ሴቶች ጋር በመወዳደር ነው።
ከዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት በተገኘ መረጃ መሠረት፡ ወደዚህ ድል ካበቋት ዋና ምክንያቶች አንዱ፡ ጨዋማ ኮረብታ የነበረውን የማይታረስ መሬት በጠንካራ ጥረት ወደ ለም የግብርና መሬት መቀየር መቻሏ ነው።
ወ/ሮ ሮዚና በቶኾንዳዕ አስተዳደር አካባቢ፡ ሩባ መሳልሕ በተባለ ስፍራ የግብርና ሥራዋን የምታከናውን ስትሆን፡ ባለትዳርና የሰባት ልጆች እናት ናት።
ይህን ቦታ ወደ ለም መሬት ለመቀየር ከልጆቼ ጋር ሆነን ከሌላ ቦታ አሸዋ፡ አፈርና ማዳበሪያ እያመላለስን ያለ እረፍት ለአሥር ዓመታት ደክመናል ስትል ትገልጻለች። በ2022 የድንች ምርጥ አምራች ተብላ በሀገር ደረጃ ተሸልማ ነበር።
