የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፖለቲካዊ ክህደት ነው ተባለ
ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ ተይዛ እንደማታውቅ አረጋገጡ።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፡ ጥቅምት 19 ፋና ብሮድካስቲንግ በአረብኛ ላቀረበው ዝግጅት ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ወደቦችንና የባሕር መስመር ይዛ እንደማታውቅ የገለጹት ሚኒስትሩ፡ ሕገ-ወጥ በነበረው የፌዴሬሽንና የውሕደት ዘመን ከነበረው ሕልውና በስተቀር የምትመልሰው ባለቤትነት እንደሌለ አስረድተዋል።
ወረራና በኃይል መግዛት ለወራሪው አካል ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ ባለቤትነት እንደማይሰጥ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፡ ይህን የተሳሳተ ትርክት የሚደጋግሙ አካላት ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
የኤርትራ ሕዝብ በ40ዎቹ ቅኝ ግዛትን የማስወገድ መብቱ በተከለከለበት ወቅት፡ ረዥምና መራራ ትግል በማድረግ ውድ መስዋዕትነት እንደከፈለ አስታውሰዋል።
የኤርትራን ነፃነት መካድና ማጥላላት፡ ሌላ የሕግ ጥሰትና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ንቀት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

