አዲስ አበባ ያልተገባ የዋጋና የቤት ኪራይ ጭማሪ ላይ እርምጃ ወሰደች
ከንቲባ አዳነች አቤቤ 500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡንና ትላልቅ የገበያ ማዕከላት እንደሚስፋፉ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን ያልተገባ የመሠረታዊ ምግብና የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውሃና የቤት ኪራይ ዋጋ መገምገሙን አስታውቀዋል።
አምራቾችንና ተጠቃሚዎችን በቀጥታ የሚያገናኙ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት በከተማዋ መግቢያዎች እየተስፋፉ መሆናቸውን፣ ምርትና ጥራትን ለማሳደግ 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡን ገልጸዋል።
የገበያ ሕግ በመጣስ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚጠናከር አስጠንቅቀዋል።
