ሚኒስትር የማነ፡ ብልጽግና ፓርቲ ራሱ የፈጠራቸውን ችግሮች ጎረቤቶቹን ይወቅሳል አሉ
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኤርትራንና ሱዳንን ከወነጀሉ በኋላ የመጣ ምላሽ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጎረቤት አገራት ኤርትራና ሱዳን አዲስ ለተመሠረተው የታጣቂና የፖለቲካ ቡድኖች ጥምር ቃል ኪዳን ድጋፍ እያደረጉ ነው ሲሉ ከወነጀሉ በኋላ፣ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ዛሬ ሰኞ መስከረም 28 በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ራሱ ለሦስት ዓመታት ያህል የፈጠራቸውን ችግሮች ጎረቤት አገራትን ይወቅሳል ያሉት ሚኒስትር የማነ፣ ይህን ለማስረዳት ሦስት ዋና ዋና ክስተቶችን በቅደም ተከተል አቅርበዋል።
አንደኛ፣ በጥቅምት ወር 2023 ፓርቲው በሰላማዊ መንገድ ሉዓላዊ የባሕር በር ለማረጋገጥ፣ አስፈላጊ ከሆነም በኃይል የሚል ዘመቻውን በይፋ መጀመሩ።
ሁለተኛ፣ በዚያው የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ተገፋፍቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላገኘችውን የሱማሊያ አካል የሆነችውን ሱማሊላንድ፣ የአንድ አገርን ሉዓላዊ መብት በመጣስ እውቅና ለመስጠት መሞከሩ።
ሦስተኛ፣ በቀጠናው የኢማራት ወኪል በመሆን የሱዳን ጦርነት እንዳያበቃ፣ የተፋጠነ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎችን በግዛቱ ወታደራዊ ሰፈር በማደራጀትና በሱዳን ሠራዊት ላይ የድሮን ጥቃቶች ለማድረስ መንገድ በመጥረግ ዓለም አቀፍ ሕግን መጣሱ።
በመጨረሻም ሚኒስትር የማነ፣ ኢትዮጵያን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ አሁንም የቀጠናው ውጥረት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።
