የዓለም የቱሪዝም ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ተከበረ
በአስመራ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ መስከረም 26 የተከበረው አጋጣሚ፣ "ዲጂታል አጀንዳና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፦ የቱሪዝምን መጪ ጊዜ መቅረጽ" በሚል መሪ ሃሳብ ላይ አተኩሯል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የዓለም የቱሪዝም ቀን መስከረም 26 በአስመራ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። የማእከል ዞን የቱሪዝም ዋና ዳይሬክተር ልያ ገብረአብ፣ ባሉት እንቅፋቶች ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ እንደታሰበው አላደገም ብለው፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዘርፉ ዕድገት ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በአጋጣሚው የቱሪዝም ሚኒስትር አስቀሉ መንቀርዮስ ተሳትፈዋል። የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማኅበር ሰብሳቢ ሰሎሞን ግርማይ ደግሞ፣ መርሐ ግብሩ የማኅበሩ አባላት የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በአጋጣሚው እስከ መስከረም 28 ድረስ የሚቆይ የፎቶ ኤግዚቢሽን፣ የቱሪዝም ተቋማት ምርቶቻቸውን የሚያሳዩበት ቦታና የሕጻናት መዝናኛ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል። ምንጭ፦ ሻዕቢት / የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር።
