ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያን ፕሬዚዳንት በአዲስ አበባ ተቀበሉ
ቪላ ሶማሊያ፣ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ የአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሶማሊያን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድን ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን ጠዋት በአዲስ አበባ ተቀብለው አነጋግረዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ቪላ ሶማሊያ በሰጠው መደበኛ መግለጫ፣ ፕሬዚዳንቱ የአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውቋል።
መግለጫው፣ የመሪዎቹ ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን ግንኙነት በማጠናከርና የቀጠናውን የጸጥታና የፖለቲካ ሁኔታ በመፍታት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል፤ ተጨማሪ ዝርዝር ግን አልሰጠም።
ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የተገናኙበት አራተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ጉብኝቱ የተካሄደው ሁለቱም መሪዎች በሀገር ውስጥና በቀጠናው ሁሉ የፖለቲካና የጸጥታ ጫና እየገጠማቸው ባለበት ወቅት ነው።

