የኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዦች ክስና ፉከራ የያዙ መግለጫዎች ሰጡ
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የውጭ ኃይሎች የታጠቁ ቡድኖችን ይደግፋሉ ሲሉ ከሰሱ፤ ጀነራል አበባው ታደሰ ደግሞ ባንዲራችንን በቀይ ባሕር ላይ እንተክላለን አሉ።

ከፍተኛ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አዛዦች፣ የውጭ ኃይሎች አዲስ የታጠቁ ቡድኖች ጥምረትን ይረዳሉና ያስተባብራሉ የሚል ክስና ፉከራ የያዙ መግለጫዎችን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማናጋትና ለማዳከም በሚደረግ ጥረት ውስጥ፣ አዲስ የተመሠረተውን የታጠቁና የፖለቲካ ቡድኖች የጋራ ጥምረት ይደግፋሉ ሲሉ ከሰዋል።
ጥረቱ ከዚህ በፊት በውጭ ድጋፍ ላይ ተመሥርቶ የነበረን ፕሮጀክት በአዲስ መልክ መቀየር ነው በማለት፣ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የሚገጥማት የጸጥታ ፈተናዎች ቀጥተኛ ወታደራዊ ወረራ የማካሄድ አቅም የሌላቸው ተብለው የሚገለጹ ወገኖች ሰፊ ስትራቴጂ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም፣ ሻዕቢያና ሕወሓት ያለ ሱዳንና ግብፅ እንዲሁም ያለ ሌሎች ኃይሎች ትእዛዝ አንድ ላይ ሆነውም ዋጋ የላቸውም፤ ተለያይተውም ትርጉም የላቸውም ሲሉ ልዩ መግለጫ መስጠታቸውን የአገሪቱ ዘገባዎች ገልጸዋል።
ሌላው ከአገሪቱ ከፍተኛ አዛዦች አንዱ የሆኑት ጀነራል አበባው ታደሰ ደግሞ፣ በዚህ ወቅት እየተከላከልን ነው፤ ጥቃት ገና አልጀመርንም፣ በምንጀምርበት ቀን ግን የመቐለ ከተማን ማዕከላዊ ጣቢያ አድርገን ባንዲራችንን በቀይ ባሕር ላይ እንተክላለን ሲሉ ፉከራ የያዘ መግለጫ አውጥተዋል።

