ኤርትራ፦ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መቋረጥ ጦርነቱን ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ የታለመ ነው አለች
አስመራ፣ ከውስጥ ቀውስ ትኩረት ለማስቀየስ የሚሠራበት የተለመደ ሰበብ ነው ብላለች።

የኤርትራ መንግሥት፣ የብልጽግና ፓርቲ ከአስመራ ጋር የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማቋረጥ የወሰደው ውሳኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት በጎረቤት አገሮች የተፈጠረ አስመስሎ በማቅረብ ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ የታለመ ነው አለ።
መልሱ የቀረበው ማክሰኞ ጥቅምት 6 በሐዳስ ኤርትራ ጋዜጣ በወጣ ሐተታ ነው።
ሐተታው፣ በአዲስ አበባ ያለው አመራር ከውስጥ የፖለቲካ ቀውስና ከጦርነት ትኩረት ለማስቀየስ የሚጠቀምበት የተለመደ ሰበብ ነው ሲል፣ የብልጽግና ፓርቲ አገሪቱን ከጎረቤቶቿ አግልሎ ራሱን የቀጣናው አለመረጋጋት ምንጭ አድርጓል ይላል።
ለአብነትም በሱዳን ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን በደል፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በመጣስ ከሶማሊላንድ ጋር ለመፈራረም የተደረገውን ሙከራ፣ እንዲሁም በኤርትራ ላይ ለዓመታት የተካሄደውን ግልጽ ዘመቻ ጠቅሷል።
በመጨረሻም፣ አሁን በኤርትራ ላይ የሚቀርበው ወታደራዊ ዛቻ ዋጋ የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ አገሪቱ ለማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጧል።
